Search

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተቋሙ ለሚገኙ መካከለኛ አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል

Published: 1 years 145 days ago

በተቋሙ መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተሰጠ ባለው ስልጠና እየተሳተፉ የሚገኙት 25 በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች ሲሆን ስልጠናው ከየካቲት 04/2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

በተቋሙ የህግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት አዘጋጀነት እየተሰጠ ያለው ስልጠና በዋናነት መሰረታዊ በሆኑ የመሪነት ጽንሰ ሀሳቦችና ተግባራት፣ በአመራር መርሆችና ቁመና፣ በአመራር ክህሎትና ብቃት እንዲሁም በስትራቴጂክ ዕቅድና ሪፖርት አዘገጃጀት ዙሪያ ያጠነጠነ እንደሆነም ታውቋል፡፡

 

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በላይሁን ይርጋ ስልጠናውን በማስመልከት በሰጡት ማብራርያ ስልጠናው በተቋሙ የሚገኙ መካከለኛ አመራሮችን የማስፈፀም ብቃት ለማሳደግ በማሰብ የመሪነት ክህሎትና ብቃት እንዲሁም በስትራቴጂክ ዕቅድና ሪፖርት አዘገጃጀት ዙርያ የተዘጋጀ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

 

አቶ በላይሁን አያይዘው አንደተናገሩት በተያዘው በጀት ዓመት ታህሳስ ወር አከባቢ በተቋሙ ለሚገኙ ሌሎች 25 መካከለኛ አመራሮች ተመሳሳይ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደርና ማህበራዊ ዋስትና ት/ት ክፍል ኃላፊና መምህር እንዲሁም በኢትዮጵያ ማናጅመንት ኢንስቲትዩት ተባባሪ አሰልጣኝ የሆኑትና በተጋባዥነት ሥልጠናውን እየሰጡ የሚገኙት ዶ/ር ተረፈ ዘለቀ በበኩላቸው መሪዎች ህዝቡንና የተቋሙን ተገልጋዮች እንዲሁም በስራቸው የሚገኙ ፈፃሚዎችን ለመምራት በቂ የሆነ ክህሎትና የአመራር ቁመና ሊኖራቸው እንዲሁም ስትራቴጂካዊ የዕቅድና ሪፖርት አዘገጃጀት ክህሎት ሊያዳብሩ የገባል ብለዋል፡፡

 

ዶ/ር ተረፈ አክለው ሲገልፁ መሪዎች ከሚመሩት አካል ጋር በቀላሉ የመግባባትና በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆነውን የተገልጋይ ፍላጎት የማርካት ብሎም የሚፈለገውን ውጤት የማስመዝገብ እንዲሁም በሥራ አከባቢ የሚፈጠሩ አለመበግባባቶችና ግጭቶችን ፈጥነው መልክ የማስያዝ ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን በዚህም ስልጠናው መሰጠቱ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡


###

training-at-fag-2019-02.jpg