Search

የአምስት ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት

Posted 298 days ago (የካ. 12, 2019 ) by SuperUser Account

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

ጥሪ ተደረገላችሁ እንግዶች

ክቡራትና ክቡራን !!

 

በቅድሚያ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የ(2011) በጀት ዓመት የአምስት ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እንዳቀርብ እድሉን ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሀገራችን የጀመረችውን ለዉጥ ጉዞ ስኬታማና ውጤታማ እንዲሆን በአሁኑ ወቅት የተቀጣጠለውን ለውጥ ዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ ለፍትህ ሥርዓቱ መጎልበትና መትጋት እንዲሁም ለህግ የበላይነትና የዜጎች ሰብኣዊ መብት መረጋገጥ ልዩ ትኩረት በመስጠት በእቅድ ዘመኑ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት የ2011 ዓ.ም መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት በየደረጃዉ ከሚገኙ አመራሮች፣ መላው ሠራተኛና ከባለድርሻ አካለት ጋር እቅዱን የጋራ በማድረግ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን በዋና ግቦችና ተግባራት ላይ በማተኮር ሪፖርቴን ለተከበረዉ ምክር ቤት በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡

 

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ

ክቡራትና ክቡራን !!

 

ተቋሙ የተሰጠውን ኃላፊነት ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመወጣትና ዕቅዱን በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ለመፈፀም የቁልፍ ተግባር መግለጫ የሆነዉን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን፡፡ ከዚህ አንፃር በ (2010) እቅድ ዘመን በቁልፍና ዓበይት ተግባራት አፈፃፀም ጥንካሬና ድክመት የለየና በጥናት ላይ የተመሰረተ የ2011 በጀት ዓመት የተቋሙን መሪ እቅድ በማውጣት ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ በዝግጅት ምዕራፉ ፈጻሚውን የማዘጋጀት ሥራ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመምራት በየደረጃው ያለውን አመራርና ፈፃሚ ለሃገራዊ ለውጡና የሕግና ፍትሕ ማሻሻያ ትግበራ ላይ የተሻለ መግባባት፣ መነሳሳትና ቁርጠኝነት አንዲሁም የሥራ ድስፕሊን እንዲፈጠር በአፈፃፀሙ የታየ ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት የግምገማና የተግባቦት መድረክ ተከናውናል፡፡ በዚህ መድረክ እንድሳተፉ ከታቀደው (1486) ፈፃሚዎችና አመራሮች ውስጥ (1211) ለማሳተፍ ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ ከግምገማና ኦረንቴሽን መድረኩ የተወሰደ ተሞክሮና ትምህርት ሲታይ በህዝባችን ዘንድ የፍትሕ ሥርዓቱ ተአማኒነትና የዜጎችን እርካታን ያላጎናፀፈ መሆኑ፣ ሥራዎችን በጥራት፣ በቅልጥፍናና በውጤታማነት ከማከናወን ረገድ ውስንነቶች መታየታቸውና እንዲሁም ደካማ የፍትህ አገልግሎት አሠጣጥን አርሞ ውጤታማ ለመሆን ከፍተኛ ርብርብ እንደሚጠይቅና በጋራ  መንቀሳቀስ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ፈጻሚ አካል ያለበትን ሁኔታ በመገንዘብ እንደተቋሙ ተናቦና ተቀናጅቶ ቀጣይ ስራዎችን በአግባቡና በላቀ ቁርጠኝነት ለመስራት የሚያስችል መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡

 

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ

ክቡራትና ክቡራን!!

 

የለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠል በተለይም የሰው ኃይል ብቃትን ከማጎልበት አንጻር የረጅምና የአጭር ጊዜ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ መሠረት በዘርፉ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል፣ የአቅም ክፍተቶችን በመለየት ከ(150) በላይ ለሆኑ የህግ ባለሙያዎች፣ ለፌዴራል ማረሚያና የፖሊስ አመራሮች በሰብዓዊ መብት አያያዝና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈፅሙ አባላት የሚኖረው የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲሁም ለ(243) ዓቃቢያን ህግ በሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር ምንነት፣ አፈጻጸምና ስላላቸው ሚና ሥልጠና መስጠት ተችሏል፡፡ የተቋሙ ተልዕኮ እንዲሳካ ለማድረግ ለሰራ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት የተሻለ አሰራርና አደረጃጀት በጥናት በመከለሰ ወደ ተግባር ለመግባት ተችሏል፡፡ የለውጥ መሳሪያዎችን ተጠቅሞ ተግባራትን ከመምራት አንጻር ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁንም ያልተሻገረናቸው በርካታ ሥራዎቸ እንዳሉ የታየ ሲሆን በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ይሆናል፡፡ በተቀናጀና ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ ከተጠሪ ተቋማትና ከፍትህ አካላት በተለይም ከፖሊስ ጋር በተሻለ መልኩ እየተሰራ ያለ ቢሆንም መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ለመገምገም ተችሏል፡፡

 

ይሁን እንጂ ቅንጅታዊ አሠራሩ እንድጎለብት ለተቋሙ ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት ጋር በዚህ በጀት ዓመት የሥራ እቅድ ውል ስምምነት በመፈራረም ሥራ ማስጀመር ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ከክልል ፍትህ ቢሮዎች ጋር የተጀመረው የጋራ መድረክና ቅንጅቱን ማጠናከር ይገባናል፡፡ የመልካም አስተዳደር አተገባበር ውጤታማነት ከማሳደግ አንጻር የውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር በመለየት ምቹ የስራ አከባቢ ለመፍጠር የሰው ኃይልና ግብአት ያለማሟላት መንስኤ የሆኑትን ጉዳዮች በጥናት ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ ይገኛል፡፡ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር በተለይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የፍትህ ሥርዓቱን የመምራትና በሁሉም ዘንድ ተአማኒነትን ለማጎልበት በተቋምና በየደረጃው ባሉ ጽ/ቤቶች በሚሻሻሉ ሕጎች ጥናትና ረቂቅ ሕግ ዝግጅት እንዲሳተፉና ግብአት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም በሕጎች አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችና ባለቤት ያለመሆኑን ችግሮችን ለመቅረፍ ዕድል የሰጠ መድረክ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

 

በተለይም ከሕግና ፍትሕ ሪፎርሞች ጋር በተያያዘ በሚሻሻሉት ሕጎች ጥናትና ረቂቅ ሕጎች ላይ ከ3000 በላይ የሚመለከታቸው አካላት ተወካዮችና ግለሰቦች እንዲሳተፉ መደረጉ ለአብነት ማሳያ ይሆናል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻልና የውጭ መልካም አስተዳደር ከማስፈን አንፃር(7705) ተገልጋዮች አገልግሎት ጠይቀው ለ(7678) ተገልጋዮች በዜጎች ቻርተር መሠረት ምላሽ ለመስጠት ተችሏል፡፡ ከአገልግሎት አሠጣጥና ከሙያ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ከውጭና ከውስጥ ተገልጋዮች (115) ቅሬታዎች ቀርበው በ (90) ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን (25) የቅሬታ ጉዳዮች በመጣራት ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

 

የተከበሩ አፈ-ጉባኤ

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

ክቡራንና ክቡራት !!

 

የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና ህዝባችን በፍትሕ ሥርዓቱ ያለውን አመኔታ ለማሻሻል በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ደረጃም ለህዝቡ ተስፋን ያሰነቁ ተግባራት ተፈፀመዋል። በርካታ ዜጎች የይቅርታ ተጠቃሚ ከመሆናቸው በላይ ጉዳያቸው በምርመራና ክስ ሂደት የነበሩት እንዲቋረጥና እንዲነሳ እንዲሁም የምሕረት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ በማፀደቅ በምህረቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑና በሃገራቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በባለቤትነት ተሳታፊ እንዲሆኑ ዕድል ተመቻችቷል።

 

Final FAG 2011 1st Qurter Parlama Report new.pdf (346.34 KB)

 

 
Final FAG 2011 1st Qurter Parlama Report new.pdf (346.34 KB)