Search

በሰዎች መነገድና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ድምበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል ቁርጠኛ አቋም ሊወሰድ የገባለ ተባለ

Published: 339 days ago

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፀረ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ግብረ ኃይል ጽ/ቤት አዘጋጅነት ከ2008 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ ያለውን አፈፃፀም የሚገመግም የግብረ ኃይሉ መደበኛ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። መድረኩም ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ እንደሆነም ታውቋል፡፡

 

እንደ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ጥናት የሀገራት በኢኮኖሚ አለመዳበር፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች፣ ሰው ሰራሽና የተፈጠሮ አደጋዎች፣ በቂ የሆነ የስራ እድል አለመፈጠር፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ተከታታይ የሆነ የግንዛቤ ማሳደግያ አሰራሮችን ዘርግቶ ተግባራዊ አለማድረግ፣ በሰዎች በሚነግዱና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሰዋችን ድምበር በሚያሻግሩ አካላት ላይ ጠንከር ያለ ህጋዊ እርምጃ አለመውስድ እንዲሁም ለጉዳዮ በቂ ትኩረት አለመስጠት ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውሮች እንዲበራከቱ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡

 

ሌሎች ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ደግሞ በየዓመቱ በሚፈፀም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በርካቶች ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶች ሲዳረጉ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች የደረሱበት እንኳ ሳይታቅ የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ በዚህም የአደጋው ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦቻቸውና የስደተኞች መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገራትም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጎጂ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

 

የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ዛሬም የተሸለ ኑሮን በማለምና ህገ-ወጥ ስደቱን ተከትሎ የሚመጣውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ቸል በማለት ወደ ተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር መቀነስ አዳጋች እንደሆነ ቆይቷል፡፡

 

ነገር ግን መንግስት በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መስፋፋት ሰበብ እየደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጉዳት ለመከላከል በአወጣው አዋጅ ቁጥር 909/2007 መሰረት ክልከላዎችን በመደንገግ ወንጀሉን ለመቆጣጠርና ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል ከ2008 ዓ.ም ጀምሮም የፌደራል ህገ-ውጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ግብረ ኃይልን በማቋቋም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

 

የተቋቋመው የፌደራል ህገ-ውጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ግብረ ኃይልም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በመንደፍ ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጥር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቋል፡፡

 

በዛሬው ዕለት በተካሄደው መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለመከላከል በየደረጃው ያለው የህግ አስከባሪው አካል በቅንጅት መስራት፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ዙሪያ መጠነ ሰፊ የሆነ የግንዘቤ ማስጨበጫ ሥራ ማከናወን እንዲሁም ህጋዊ ስምሪቱን በማሳለጥ ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋምና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብን የመበጣጠስ ሥራ በተጠናከረና ስትራቴጂክ በሆነ መልኩ ሊሰራ ይገባል ብለዎል፡፡

 

በማያያዝም ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙርያ ጥናቶች እና ምርምሮች ሊካሄዱ፣ የተገኙ ውጤቶችም ጥቅም ላይ ሊውሉ ይገባል ብለዎል፡፡

 

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፀር ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ግብረ ኃይል ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ መሳይ ፀጋዬ በበኩላቸው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደተኞችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ግብረ ኃይሉ የአምስት ዓመት ስትረቴጂክ ዕቅድ በመንደፍ ለአዋጁ ተግባራዊነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

 

በመድረኩ እንደተባለው ከጉዳዩ ስፋት አንፃር የተመዘገበው ውጤት አበረታች ቢሆንም በተለይ ግንዘቤ የመፍጠር ተግባራት በተከታታይነት አለመተግበር፣ በመነሻና ድንበር አከባቢ በሚገኙ የመወጫ በሮች የሚደረግ ቁጥጥር አናሳ መሆን፣ ከስደት ተመላሾችን መልሶ የማቋቋም ተግባር በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው ከመስራት አንጻር ውስንነቶች የሚታዩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

 

በመሆኑም በተደረገው የአፈጻጸም ግምገማና ጥናት መሰረት በቀሪው የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም ስትራቴጂክ ዕቅዱን ከልሶ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ መድረግ ይቻል ዘንድ ግብረ ኃይሉ ዛሬ ቀኑን ሙሉ ሲመክር ውሏል፡፡


###

52882843_2125766370850769_1527562430865997824_n.jpg  53012111_2125766237517449_3376840155838021632_n.jpg  52596551_2125766274184112_94830910800658432_n.jpg