Search

ዐቃቤ ሕግ ቴዎድሮስ አዲሱ(ቴዲ ማንጁስ) ባቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ምላሽ ሰጠ

Published: 306 days ago

ቴዎድሮስ አዲሱ ወይም በቅጽል ስሙ (ቴዲ ማንጁስ) ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር በተያያዘ ሁኔታ ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚውሉ 578,274 የመማሪያ መጽሐፍቶችን በግዥ ለማቅረብ በሚል ሰበብ በተፈመ የሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉና ክስ የተመሰረተበት መሆኑ ይታወሳል፡፡

 

ሆኖም ተከሳሹ ድርጊቱ የተፈፀመው በሶማሌ ክልል በመሆኑ የፌዴራሉ መንግስት ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም፣ የክሱ ጭብጥ የሚያሳስትና ግልፅ አይደለም እንዲሁም ተላልፋችኻል የተባልንበት መመሪያዎችና ስነ - ስርዓቶች ግልፅ አይደሉም በማለት ፍርድ ቤቱ ክሱን እንዲያቋርጥ አልያም ዐቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል በመጠየቅ የቀረበበትን ክስ ተቃውሞ ተከራክሯል፡፡

 

ዐቃቤ ሕግ ለቀረበበት የክስ መቃወሚያ ዛሬ ለዋለው ችሎት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 25/88 አንቀፅ 4(11) መሰረት በክልሎች ወይም በፌዴራልና ክልል ስልጣን ስር የተከናወኑ የወንጀል ድርጊቶች የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የመዳኘት ስልጣን እንዳላቸውና በተጨማሪም ከሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በልዩ ሁኔታ በአዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀፅ 4(1) እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 883/97 አንቀፅ 6(ሀ) መሰረት ከፌዴራል ድጎማ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በፌዴራል ደረጃ መታየት የሚችሉ መሆናቸውን አብራርቷል፡፡

 

በአዋጅ ቁጥር 883/2007 አንቀፅ 6 መሰረት ከአንድ በላይ በሆኑ ክልሎች በሚንቀሳቀሱ ህዝባዊ ድርጅቶችና ሰራተኞች የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀል ድርጊቶች በፌዴራል መንግስት ስር የሚዳኙ መሆኑን በማብራራት ወንጀሉ በኒያላ ኢንሹራንስ ሶማሌ ቅርንጫፍ አማካኝነት የተፈፀመ በመሆኑ ዳኝነቱ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች መታየት ይችላል ብሏል፡፡

 

በተጨማሪም የመጽሐፍቱ ግዥ በጀት ከፌዴራል መንግስት ለክልሉ ከሚሰጥ ድጎማ ጋር የተያያዘና በበጀቱ ላይ የፌዴራል መንግስት ድጎማ መኖሩን የሚያሳይ ማረጋገጫ በመኖሩ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽን የመክሰስና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ደረጃ እንዲዳኝ የማድረግ ስልጣን እንዳለው በማብራራት ተከሳሽ ያቀረበዉ የክስ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

 

በመቃወሚያው ላይ የክሱ ሁኔታ ግልፅ አይደለም በማለት ተከሳሽ ላቀረበው ሀሳብ ከትምህርት ቢሮ ጋር ውል ሲገባ ያለ በቂ ማስያዣ መፈፀሙና ማስያዣ የነበረ መሆኑን ለማስመሰል በደረቅ ቸክ ተዘጋጅቶ መፈፀሙና የቀረበው ደረቅ ቸክ ዋስትና በተገባለት ያለአግባብ ከትምህርት ቢሮ በተከፈለ ገንዘብ የተከፈተ አካውንት ነው በማለት ዐቃቤ ሕግ በመልሱ አብራርቷል፡፡

 

በተጨማሪም በተከሳሽ በኩል የተጣሱ ህጎችና ድንጋጌዎች በክሱ ላይ በግልፅ አስቀምጫለሁ ተከሳሽ የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/ 1(ሀ፣ለ)ና አንቀፅ 33 እንዲሁም በሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 13(1ሐ)ና አንቀፅ 2 በተደነገገው መሰረት መከሰሳቸውንና የኢንሹራንስ አሰራርና ዋስትና አሰጣጥ መመሪያ በመጣስ እንዲሁም በትምህርት ቢሮ አሰራር፣ የግዥ ሕጎችና የስራ መዘርዝሮችን መሰረት ያላደረገ ውል መዋዋላቸውን ዐቃቤ ሕግ በመልሱ አብራርቷል፡፡

 

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎት በዛሬ ውሎው የተከሳሽን መቃወሚያና የዐቃቤ ሕግን መልስ በመመርመር መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ብይን እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

 


###

fb_img_1532892211511.jpg