Search

ከመጋቢት እስከ መጋቢት የፍትህ ስርአቱ የለዉጥ ጉዞ በኢትዩጵያ

Published: 294 days ago

ከመጋቢት እስከ መጋቢት የፍትህ ስርአቱ የለዉጥ ጉዞ በኢትዩጵያ፡

የአዲሰቷ የተሰፋ አድማስ ብሰራት

 

መጋቢት 2011 ዓ.ም

አዲስ አበባ

 

    

1. መግቢያ

 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም እስከ መጋቢት 2011 ዓ.ም በአንድ አመት ጊዜ ዉስጥ በርካታ ተግባራትን በማከናወን የፍትህ ሪፎርሙን የለዉጥ ጉዞ የተሻለ ዉጤት እንዲያስመዘግብ ላቅ ያለ ሚናዉን ተወጥቷል፡፡

 

በዚህም መሰረት የህግና የፍትህ ምህዳሩን ለማስፋትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የቆመላቸው ዋና ዋና ዓላማዎች ህገ መንግስቱን እና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ማክበርና ማስከበር፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የወንጀል ህግን ማስከበርና የፌዴራል መንግስቱን እና የህዝብን የፍትሐ ብሄር ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ተቋማዊ ለውጦችን አከናውኗል፡፡

                                               

2. የተከናዉኑ ዋና ዋና ጉዳዮች

 

2.1. የጋራ መግባባት የመፍጠር፣የዕቅድና የዝግጅት ተግባራት

 

የ2011 ዓ/ም በጀት ዓመት ዕቅድ ዘመን በተለየ መልኩ  በሃገራችን እየተካሄደ ያለውን ሃገራዊ ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሕግና ፍትሕ ስርአቱን በማሻሻል፣የፍትሕ ስርዓቱ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ የዜጎች ሰብኣዊ መብትና ክብር የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ፣ የህዝባችን የፍትሕ ፍላጎትና ጥያቄዎች ያለአድልዎ፣ በፍትሃዊነትና በዕኩልነት መርህ የሚመልስና የህዝባችን እርካታና  አመኔታ ያረጋገጠ  የሕግና የፍትሕ ዘርፍ እንዲሆን መንግስት በወሰነው የማሻሻያ ዕርምጃ መሰረት በሰራተኛው ከፍተኛ የለውጥ ስሜትና መነሳሳት ለመፍጠር፣ በማሻሻያው አስፈላጊነትና በዕቅዱ ግቦች፣ተግባራትና የአፈፃፀም አቅጣጫዎች የጋራ መግባባት ለመድረስ ወሳኝ የዕቅድ ዘመን በመሆኑ መላው ሠራተኞች፣የተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣የተወሰኑ የሕብረተሰብ አባላትና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በጥናት የተመሰረተ ዝርዝር ግምገማና ሰፊ የመግባብያ መድረክ ተካሄዷል።

 

የመግባብያ መድረኩ በጥናት በተለዩ የህዝቡን እርካታና አመኔታ ለማረጋገጥ እንቅፋት የሆኑ የሕግና ፍትሕ ችግሮች ከመቅረፍ፣የተቋሙ ዋናዋና ተልእኮዎች ከማሳካት አንፃር የነበረው የአፈፃፀም ደረጃውና በተለይም በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ማክበርና የማስከበር እንዲሁም የሕግ የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ ተቋሙ፣ግለሰብ ዐቃቤ ሕጉና ሌላው ሰራተኛ የነበረው ሚና ማዕከል በማድረግ የተካሄደ ነው፡፡

 

በተለይም ደግሞ በሃገራችን እየተካሄደ ያለውን ሃገራዊ ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሕግና ፍትሕ ስርአቱን ለማሻሻል ሊውሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በስፋት ወይይት ተደርጎበታል፡፡ 

 

በሃገራችን የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ሰላም ለማስፈን፣ ልማትና እድገትን ለማፋጠን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ጥረቶች እየተደረጉ እንደነበርና በፍትሕ ስርአቱ የተመዘገቡ የተወሰኑ ውጤቶችም የዚሁ አገራዊ ጥረት አካል መሆናቸው፣ይሁን እንጂ ከመንግሰትና የህዝብ እርካታና አመኔታ እይታ አንፃር የፍትሕ ስርአቱ አጠቃላይ አፈፃፀም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ ህዝባችን በተደጋጋሚ የተማረረበት፣የሕግ የበላይነት ትርጉም ያጣበትና የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደታችን ፈተና ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ፈጥሮ አንደነበረ መግባባት ተደርሷል፡፡

 

በነዚህ መድረኮች በዋናናት ከተለዩ አንኳር ጉዳዮች መካከል፡-

 

1.የፍትሕ ስርዓቱ ነጻና ገለልተኛ በመሆን የሕግና የፍትሕ ጉዳዮችን የህዝብን ፍላጎትና ጥያቄዎች በሚመልስ ደርጃ አለመሆኑ፣

 

2. የሕግ አስከባሪ ተቋማት ለፍትሕ ታማኝ፣ ለዜጎች መብት ቀናኢ እንዲሆኑ የሕዝባችን ፍላጎት ቢሆንም ተቋማቱ ይህንን ፍላጎት በሚያሳካ ቁመና ላይ አለመሆናቸው፣

 

3. የሕግ አወጣጥ፣ አፈፃፀምና አተረጋጎም ስርአቱ አሳታፊነት የጎደለው፣ሕግ ሁሉንም በዕኩል በመዳኘትና ዜጎች በተፈጥሮ ያላቸውን ሰብዓዊ ክብርና መብት በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑ፣

 

4. የሕግና የፍትሕ ስራችን ዜጎች በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን ሰብአዊና ድሞክራሲያዊ እንዲሁም ፍትሕ የማግኘት

መብታቸውን ለማረጋገጥና ጥሰቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ደካማ ሆኖ የቆየ መሆኑ፣

 

5. ከሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ የተያዙ፣የተከሰሱና የተፈረደባቸው ሰዎች አያያዛቸው ሰብአዊ ክብራቸው በተጠበቀ መልኩ ሕገ

መንግሰቱ ባሰቀመጠው መሰረት አለመሆኑ፣

 

6. የሚወጡ ሕጎች በሕገ-መንግስት እዉቅና የተሰጣቸዉ የዜጎች መሠረታዊ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶችን በተሟላ ያላከበሩ፣

 

7. የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስጠብቁ አለመሆናቸዉና መብቶችን በመገደብ በዜጐች ላይ የመብት ጥሰት አድርሰዋል በማለት

በህብረተሰቡ ነቀፌታና በተጋጋሚ ጥያቄ የሚቀርብባቸው ህጎች እንዲወጡ ምክንያት መሆኑን፣

 

8. የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ዲሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ ያልተሻገርናቸው በርካታ ፈተናዎች እና ችግሮች  በመኖራቸው ሕብረተሰቡ ችግሩን ሊሸከመው በማይችል ደረጃ በመድረሱ ለሰላማችን መደፍረስ፣

 

9. በመላ አገሪቱ አለመረጋጋት ተፈጠሮ መደበኛው የሕግና ፍትሕ ስርአት አመኔታ አጥቶ ስርአት አልበኝነትና የመንጋ ፍትሕ በመስተዋሉ የህዝባችንና የአገራችን ህልውና ለአደጋ ተጋልጦ መቆየቱ፣

 

10. የፍትሕ ስርአቱ ድክመት ማሳያ መሆኑንና በተመሳሳይ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሕግ የማስከበርና ሕግ የማስፈጸም ተልዕኮአችን ፍትሓዊነት የጎደለውና ሰፊ ክፍተት እንዳለው ግንዛቤ እንዲያዝበት ተደርጓል።  በዚህ ረገድም መግባባት ተፈጥራል፡፡

 

ስለሆነም ይህን ሁኔታ ከመሰረቱ ለመቀየር መንግስት እራሱን በጥልቀት ፈትሾና የአመራር ለውጥ በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ሪፎርም ለማካሄድ ወስኖ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆኑ፣ በተለይም የሕግ የበላይነት ዕውን እንዲሆን አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በመንግስት ቁርጠኛ አቋም መያዙንና የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ግልፅነት ተፈጥሯል ፡፡  

 

በዚሁ መሰረት ምን ሰራን ? ምንስ ለዉጥን ? በዚህ የአንድ አመት የለዉጥ ጉዞ ወሰጥ እኛ የት ነዉ ያለነዉ ?

 

2.2. የአሰራርና አደረጃጀት ማሻሻያና የሰው ሃይል ብቃት ማሳደግ

 1.  

የለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠል፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ተልእኮ ለማሳካትና የፍትህ አግልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የአሠራርና አደረጃጀት የማሻሻል እና የሰው ኃይል ብቃት የማጠናከር እንዲሁም በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ የስነምግባር ጉድለት፣ የሙስና፣ አድሏዊና ብልሹ አሰራሮች ህዝብን በማሳተፍ በመታገል ተቋሙ የህብረተሰብ አመኔታ ያተረፈ እንዲሆን ለማድረግ የመዋቅሩን አቅም በተለይም የሰው ኃይሉን ብቃት መገንባትና አገልግሎቶች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የማስደገፍ ሥራዎች ተጠናክረው መሠራት እንዳለባቸው ቁልፍ ተግባር ሆኖ በዕቅዱ ተካቷል ፡፡

 

በርካታ አዳዲስ ተቋማዊ የአሠራር ሥርዓቶችን በመቀረፅ የነበሩ አሠራሮችን በመፈተሽና በመከለስ እንዲሻሻሉ ተደርጓል፡፡የማነጅመንት አሰራር የተከለሰ ሲሆን የዓቃብያነ ሕግ የዓቃብያነ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በማስፀደቅ በህትመት ላይ ይገኛል፡፡ የሙያ ስነምግባር ደንብ ለማስፀደቅና ለመተግበር፣ የደንቡ ማስፈፀምያ መመርያዎች ለአብነት የምልመላና ሹመት፣ የዝውውር፣ የደረጃ ዕድገት፣ የስራ ቦታ ድልድል፣ የስራ አፈፃፀም ምዘና፣ …ረቂቅ መመርያዎች በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን፡፡

 

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሌሎች ተቋማት ይሠሩ የነበሩ የዐቃቤ ሕግ ሥዎችን በማሰባሰብ እራሱን ሲያደራጅ የቆየ ቢሆንም ተቋሙ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት ቁልፍ ማነቆ የነበሩ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥርዓቱን ጥናት በማካሄድ የዘርፍ አመራር እንዲኖርና በሦስት ተቋማዊ ዘርፎች እንዲዋቀር፣ ሊዋሃዱና ሊታጠፉ የሚገባቸውን ዳይሬክቶሬቶችና የተቋሙ የውስጥ አደረጃጀት እንዲስተካከሉ ተደርጓል፡፡

 

በዚሁ መሰረት በምክትል ጠቅላይ ዐቃብያነ ሕግ የሚመሩ ሶስት ዘርፎች፣ 20 ዳይሬክቶሬቶች፣ 5 ጽ/ቤቶች እና 11 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መልሶ ተደራጅተዋል፡፡ ስራዎችን በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ለመምራት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የሚመራ ሁሉንም የበላይ አመራሮችን ያካተተ በቁጥር የተመጠነ የማኔጅመንት ኮሚቴ እና በዘርፍ አመራሮች የሚመራ የንዑስ ማኔጅመንት ኮሚቴ ተደራጅቶ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

 

ያለበቂ ጥናት በክልሎች ተከፍተው የነበሩ ቅ/ፅ/ቤቶች ከውጤታማነት፣ ተደራሽነትና ወጪ ቆጣቢነት አንፃር በጥናት በመገምገም ለጊዜው እንዲታጠፉ ተደርጓል፡፡ በተሻሻለው  አደረጃጀት መሰረት የአመራርና የሰው ኃይል ድልድልና ሥምሪት ተካሂዷል፡፡ የተሻለ ብቃት ያላቸውን ዐቃብያነ ሕግን በመለየት በዝውውርና የአስዳደር ሰራተኞችን በቅጥር የሟሟላት ተግባር ተፈጽሟል፡፡ በተቋሙ ውስጥ 241 (29%) ሴትና 599 (71%) ወንድ በድምሩ 840 ዐቃብያነ ሕግ እንዲሁም 425 (64%) ሴትና 244(36%) ወንድ በድምሩ 669  የአስተዳደር ሰራተኞች በአጠቃላይ 1439 ሰራተኞች ስራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

 

ካሉት የኃላፊነት ቦታዎች (27%) የሴቶች የአመራርነትና የኃላፊነት ቦታ እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡ የሰው ኃይል ብቃትን ከማጎልበት አንጻር የረጅምና የአጭር ጊዜ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረናል፡፡ በዚህ መሠረት በዘርፉ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል የመጠቀምና የአቅም ክፍተቶችን በመለየት ከ150 በላይ ለሆኑ የሕግ ባለሙያዎች፣ ለፌዴራል ማረሚያና የፖሊስ አመራሮች በሰብዓዊ መብት አያያዝና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈፅሙ አባላት የሚኖረው የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲሁም ለ243 ዓቃቢያን ሕግ በሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር ምንነት፣ አፈጻጸምና ስላላቸው ሚና ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

 

ሆኖም ልምድ ያለው ሰራተኛው በተቋሙ እንዲቆይና የተሻለ ብቃት ያለው ለመሳብ፣ የህዝብ አገልጋይነት ስሜት ተላብሶ ሥራን በተነሳሽነትና በባለቤትነት ለመስራት እንዲቻል የተመቻቸ የስራ ሁኔታ የመፍጠርና የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ በክትትልና ድጋፍ፣ በሥልጠናና ልምድ ልውውጥ ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት ይጠይቀናል፡፡

 

ቅንጅታዊ አሠራር ከማጠናከር እና ከማጎልበት አንጻር ከተጠሪ ተቋማትና ከፍትህ አካላት በተለይም ከፖሊስ ጋር የጋራ ዕቅድ በማውጣት በተሻለ ቅንጅት እየተሰራ ሲሆን ለተቋሙ ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት ጋር በ100 ቀን ዕቅድና የሥራ እቅድ ስምምነት በመፈራረም ሥራ የጀመርን ሲሆን በዚሁ መሰረት ስለመፈጸሙ የ5 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በመገምገም የቀጣይ ስራ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

 

ከተጠሪ ተቋማት ጋር የሚኖረንን በቀጣይ ግንኙነት የሚመራበት የክትትል፣ ድጋፍና ሪፖርት ሰርዓት በመዘርጋት የተጠናከረ ስራ ማከናወን እንደሚገባ የጋራ ግንዛቤ የተያዘ በመሆኑ ይህን አጠናክረን ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ የክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋማት/ፍትሕ ቢሮዎች  ከመደገፍ አኳያ አጥጋቢ ባለመሆኑ የተጀመረው የጋራ መድረክና ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር  አንድ የጋራ ምክክር መድረክ ለማካሄድ ተችሏል፡፡

 

2.3. የተመቸ የስራ አከባቢ ለተገልጋይና ለሰራተኛው መፍጠር

 1.  

የውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር በመለየት በጥናት ምላሽ ለመስጠት፣ ምቹ የስራ አከባቢ ለመፍጠርና የግብአት አቅርቦት ለማሟላት  ሶስት ኮሚቴዎች በማደራጀት ግብአት የማሟላት፣ የህንፃ አድሳት፣ የባጅ፣ መታወቅያና ሌሎች ፈጣን ምላሽ አምጪ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ የግብዓት ማነቆን ለመፍታትም የግዢ እቅድ  በማውጣት ግዢ እንዲፈጸምና እንዲሟላ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

 

2.4. የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ የዲሞክራሲ ስርአቱን ማጎልበት

 1.  

በመንግስት በሃገራችን የሕግ የበላይነት አለመረጋገጡና በሕግና በፍትሕ ስርአቱ ደካማነት  የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ጥሰት ማስከተሉና ህዝቡ በመንግስትና በፍትሕ ስርአቱ አመኔታ ማጣቱ የዕቅዶቹ ዋነኛ መነሻ ተደርጎ ተወስዷል፡፡በመሆኑም የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና ህዝባችን በፍትሕ ሥርዓቱ ያለውን አመኔታ ለማሻሻል በመንግስት ከተወሰደው የማሻሻያ እርምጃ በተጨማሪ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ደረጃም ለህዝቡ ተስፋን ያሰነቁ ተግባራት ተፈፀመዋል።

 

በርካታ ዜጎች የይቅርታ ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ ጉዳያቸው በምርመራና ክስ ሂደት የነበሩት እንዲቋረጥና እንዲነሳ እንዲሁም በሃገራችን ለመጀመርያ ጊዜ የምሕረት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ በማፀደቅ በምህረቱ 45,875 ግለሰቦች ተጠቃሚ እንዲሆኑና በሃገራቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በባለቤትነት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደረገዋል። 

 

የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሀ ግብር አፈፃጸም ከመከታተል ተግባር ጎን ለጎን የመብት ጥሰትን ለማረም የተያዙ፣ የተከሰሱና የተፈረደባቸው ሰዎች አያያዛቸው ሕገ መንግሰቱ ባሰቀመጠው መሰረት ሰብአዊ ክብራቸው በጠበቀ መልኩ እንዲፈፀም በማረምያ ቤቶች ጉብኝት በማድረግ ህገ ወጥ ተግባር እንዲታረምና ሕግን በተላለፉ ሰዎች በሕግ መሠረት እርምጃ የመውሰድና ከዚህ ጋር በተያያዘ መሠረታዊ ችግር ያለባቸውን አመራሮች የመለወጥና ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ ተከናውኗል፡፡

 

የፍትህ ሥርዓቱን የግልፅነትና ተጠያቂነት አሠራር ከመዘርጋት በተጨማሪ ሁሉም ተግባራት ሰብዓዊ መብትን ባከበረ አግባብ በተጠያቂነት መንፈስ እንዲተገበሩ የማስገንዘብና የተያዙ፣የተከሰሱና የተፈረደባቸው ሰዎች አያያዛቸው ሕገ መንግሰቱ ባስቀመጠው መሰረት ሰብአዊ ክብራቸው በተጠበቀ መልኩ  እንዲሆን ጥረት ተደርጓል ፡፡ በዚህም በተግባር በዘላቂ እምነት መቀየር ያለበት መሻሻል ማሳየቱና ለዚህም በቅርቡ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች ምስክርነታቸው የሰጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

 

የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተለይም ተጠያቂነትን ከማሰፈን አንጻር የወንጀል ሕጉን በማስከበር የወንጀል ፍትህ አስተዳደሩን ውጤታማነት ለማሳደግ ሠፊ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ለአብነት፡-

 •  

1. በሰብአዊ መብት ጥሰት እና ከባድ የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ የመንግስት ባለስልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተከናወነ ሲሆን የምርመራ ሥራውን አስቀድሞ ጥናት በማካሄድና ተጠርጣሪዎች ሳይያዙ በማጣራት ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው በቂ ምክንያት መኖሩን በማረጋገጥ ለሕግ አንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡  ተጠርጣሪዎቹን ለሕግ የማቅረብ ሂደቱ በሕገ መንግስቱ መሠረት ሰብአዊ መብታቸውን በጠበቀ፣በሕግ አግባብ በፍርድ ቤት ዕውቅናና ትእዛዝ እየተከናወነ ሲሆን ማስረጃዎችን የማጠናከርና እስካሁን በሕግ ቁጥጥር ሥር ያልሆኑ ተጠርጣሮችን በመያዝ ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ አንዳንዶቹ ላይ ክስ እንድመሰረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

 

 • 2. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ የመጡ የወንጀል ተግባራት በተለይም በብሔር ወይም በክልሎች መካካል በግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጠር ግጭት መነሻነት በመፈጸማቸው ምክንያት ወንጀሉ የተፈጸመባቸው አከባቢዎች በክልሎች ትብብርና ከፖሊስ ጋር በጋራ በመቀናጀት ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉና የተደራጀ የምርመራና ክስ በመመስረት ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ መሰረት፣
 •  
 • 2.1. በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ጌደኦ ዞን አንዳንድ አከባቢዎች፣
 •  
 • 2.2. በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በጅግጅጋና ሌሎች ዞኖች የተፈጸመውን ወንጀል፣
 •  
 • 2.3. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል በክልሉ ከሰኔ 18/2010 ዓ.ም ጀምሮ በአሶሳ እና አካባቢው ብሔርን መሰረት በማድረግ ከበርታ ብሄረሰብ ውጭ ያሉትን ሰዎች በመለየት በተፈጸመው ወንጀል፣
 •  
 • 2.4. በደቡብ ክልል  በሀዋሳ ማረሚያ ተቋም ውስጥ እና በሀዋሳ ከተማ /ማረሚያ ተቋም ውጭ / የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት፣
 •  
 • 2.5. በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ከተማ በተመሳሳይ በብሔር ማነሳሳትና መነሳሳት የግድያ፣ የቃጠሎ፣ የከባድ ውንብድናና የመሳሰሉ ወንጀሎች፣
 •  
 • 2.6. በአዲስ አበባ ከተማም በተመሳሳይ ፍላጎትና ሀሳብ ብሔርን መሰረት በማድረግ ልዩልዩ ወንጀሎች፣
 • ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ለመግደል ታስቦ የተፈጸመውን ወንጀል
 •  
 • 3. በአጠቃላይ ከላይ እንደተጠቀሰው በክልሎች ትብብርና ከፈዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመቀናጀት ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉና የተደራጀ የምርመራ በማድረግና ክስ በመመስረት ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡

 

 • ከዚህ በተጨማሪ ሕገ ወጥ የጦር መሳርያ፣የገንዘብ ዝውውርና የቴሌኮም ማጭበርበረን ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎች ለሕግ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት የተጀመሩ ሥራዎች ያሉ ቢሆንም ከወንጀሉ ስፋትና ውስብስብነት አኳያ በቀጣይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ልንሰራበት እንደሚገባ ግንዛቤ ተወሰዷል፡፡
 •  
 • 2.5 የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አፈጻፀም ማሻሻል
 •  

የዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገብና የክስ ውሳኔዎች በተፋጠነና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲፈጸሙ ማድረግ፣ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱንና የህዝብ ጥቅምን አደጋ የሆኑ ከባድ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ቅድሚያ በመስጠት፣በተፈጸሙ ወንጀሎችንም ወንጀል አድራጊዎቹን ተገቢ ቅጣታቸውን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ንጹሀን እንዳይጎዱ መከላከል፣ የወንጀል ሰለባዎች ለደረሰባቸው ጉዳት የሚካሱበት ሥርዓት መዘርጋት፣ ታራሚዎች ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ ታርመውና ታንጸው ሕግ አክባሪና አምራች ዜጋ ሆነው እንዲወጡ ቅንጅታዊ አሠራሩና አደረጃጀት የማጠናከር የሚስችል በርካታ ተግባራት ተከናዉናል፡፡

 

በዚህም በአገልግሎት አሰጣጡ ተደራሽነት፣ቅልጥፍናና ውጤታማነት መሻሻል ላይ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በተለይም ከምርመራ መዝገብ የውሳኔ አሰጣጥ ቅልጥፍና (የማጥራት ምጣኔ)፣ከክስ ውጤታማነት (የማስቀጣት ምጣኔ) እንዲሁም በምስክር አለመቅረብ የሚቋረጡ መዝገቦች መቀነስ (የመንጠባጠብ ምጣኔ) ላይ ካስቀመጥነው ግብ አንፃር ጥሩ አፈፃፀም ተመዝግባል፡፡ የከባድና ውስብስብ ጉዳዮች ምርመራ ውጤታማ ለማድረግ በተለይም በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀሎች ምርመራው ከፖሊስ ጋር በማካሄድ ዐቃቤ ሕግ በመዛግብት ለመወሰን በቡድን ውይይት በማድረግ ከኃላፊዎች ጋር በመመካከር መወሰን እንዳለባቸው ስርዓት ተዘርግቶ በዚህም የተሻለ ውጤት ታይቷል፡፡ በተለይም ከቅልጥፍና አንጻር የዐቃቤ ሕግ የመወሰን አቅም ተሻሽሏል፡፡ በሴቶችና ህፃናት የሚደርሱ የልዩ ልዩ ወንጀሎች አፈጻጸም ቅልጥፍናና ውጤታማነት ለማሻሻልም ጥረት ተደርጓል፡፡

 

2.6. የሕግና ፍትሕ ስርአት ስራ ማሻሻያ አፈፃፀም

 1.  

መንግስት የሕግና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻልና በዘርፉ አሳታፊነትን ለማጎለበት በሰጠው ትኩረት መሠረት ከመንግስት መዋቅር ውጭ ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸውን የሕግ ባለሙያዎች ያካተተ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ በማቋቋም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ አማካሪ ጉባዔው የማሻሻያ ሥራውን የሚመራበት፣ ዓላማውንና የትኩረት አቅጣጫውን የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ፣ እንዲሁም በማሻሻያ ሥራው የባለድርሻ አካላትና የህዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚረዳ የህዝብ ተሳትፎ ስትራቴጂ ሠነድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

 

አማካሪ ጉባዔውን ለማጠናከር ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የማስተዋወቅ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች እውቅና ሰርተፊኬት የመስጠና የተጓደሉ አባላትን የማሟላት ተግባር ተከናውኗል፡፡ በሥራ ላይ ያሉትን ህጎችና አተገባበር በጥናትና የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ለማሻሻል የህጎቹን አተገባበር የሚገመግም ጥናትና በጥናቶቹ ግኝት ተከታታይ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮች በማካሄድ ከተገኘው ግብዓት በመነሳት ረቂቅ ሕግ የማዘጋጀትና በረቂቅ ህጎችም ላይ ግብዓት የማሰባሰብ ተግባር ተከናውኗል፡፡ በዚሁ መሰረት፡-

 

 • 1. የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ፣
 •  
 • 2. ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ማሻሻያ አዋጅ፣
 •  
 • 3. የንግድ ሕግ
 •  
 • 4. የጠበቆች አዋጅ፣
 •  
 • 5. የምርጫ ሕግ፣
 •  
 • 6. የጦር መሳሪያ አያያዝና አስተዳደር አዋጅ፣
 •  
 • 7. የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፣
 •  
 • 8. የኃይል አጠቃቀም አዋጅ በወይይት መድረኮች የሚዳብሩ የሕግ ማዕቀፎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ ከተከናወኑ ረቂቅ ሕጎች መካከል አንዱ የመደራጀት መብትን የተመለከቱ አለም ዓቀፍና አህጉራዊ፣ እንዲሁም ሕገ-መንግስታዊ መርሆዎችን ባገናዘበ መልኩ
 •  
 • 9. የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች አዲስ  ሕግ በተወካዮች ምክር ቤት  ፀድቆም በሥራ ላይ እንደሚውል ተደረገዋል፡፡
 •  
 • 10. በተመሳሳይ የፀረ ሽብርተኝነት ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀ ሲሆን አማካሪ ጉባኤው ረቂቅ አዋጁን በመገምገም ተገቢ ግብዓት ከተሰበሰበበት በኃላ በቅርቡ ለሚመለከተው አካል ይቀርባል፡፡ 
 •  

በሌላ መልኩ የሕግ የበላይነት የተጠናከረበት የፍትህ ሥርዓት እንዲኖር ጠንካራ የሆነ የሕግ ባለሞያዎች አስተዳደር የሕግ ማዕቀፍ ጥናት እንዲጠናቀቅ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የአስተዳደርና የሕግ ማውጣት ሥነ-ሥርዓትን ለማሻሻል በተለይም ለአስተዳዳር ሥነ ሥርዓት ሕግ ትኩረት በመስጠት በተለያዩ ተቋማት የተዘጋጁ ረቂቅ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕጐችን በመገምገም ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡

 

ለረጅም ጊዜ በሥራ ላይ የቆየውን የንግድ ሕግ ለማሻሻል ከዚህ ቀደም የተጀመረው ሥራ ተጠናቆ የተዘጋጀ ቢሆንም ሕጉ ለሀገሪቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ በኮድ መልክ የሚዘጋጁ ህጐች ሊኖራቸው የሚገባውን ዘመን ተሻጋሪ ባህሪና የንግድ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ድንበር ተሻጋሪ እየሆነ መምጣቱን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ረቂቁን መከለስና ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚሁ መሠረት ረቂቅ የንግድ ሕግ ኮዱን በዝርዝር እየገመገመ ሲሆን ከዓለም ዓቀፍ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የክለሳ ሥራውን በማካሄድ ላይ እንገኛለን፡፡

 

የወንጀል ፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸውን ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግና ማረሚያ ቤቶች ተቋማዊ ሁኔታ የሚገመግም የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ የማረሚያ ቤት ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ የሰብዓዊ መብቶችንና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ባገናዘበ መልኩ በመከለስ ሂደት እገዛ እየተደረገ ሲሆን ረቂቅ አዋጁ በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚቀርብ ይሆናል፡፡

 

በሌላ መልኩ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የሰብዓዊ መብቶችን በሚያስከብር መልኩ እንዲከለስ የተደረገ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተሻሻለ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡

የዲሞክራሲ ተቋማት ማሻሻያ በሚመለከት በቅድሚያ ለምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት በምርጫ ህጐችና በዳሰሳ ጥናት በተለዩ አራት ርዕሶች ማለትም የምርጫ አስፈፃሚው፣ ከምርጫ ግጭቶች አፈታት፣ የምርጫ ሥርዓትና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመዘጋገብ ላይ ጥናት ተካይዷል፡፡

 

የምርጫ ቦርድን አወቃቀር ጥናት ላይ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮች ተካሂደው የምርጫ ቦርድን እንደገና ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ምክክር ተደርጎበታል፡፡ በተመሳሳይ የሚዲያ ሕጐችን ለማሻሻል የሕግ ማርቀቅ ሥራ በመጀመር የባለድረሻ አካላት የመጀመሪያ ዙር የምክክር መድረክ ተከናውኗል፡፡ በምክክር መድረኩም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ በመሆናቸው የሕጎችን የማርቀቅና የማሻሻል ተግባራት ላይ አሣታፊ መደረጉ የፍትህና ሕግ ሪፎርም ሥራዎቻችን ላይ አዎንታዊ አሰተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

 

በቀጣይ የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖርና ህጎች የተነሡበት ዓላማ በሚያሳካ አኳኃን እንዲፈፀሙና እንዲተረጎሙ በማድረግ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ትኩረት የሚሠጠው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካት የማስፈጽም አቅምን በመገንባት ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት፣ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሣትፎ በማጎልበት ሕግና ሥርዓት የሚያስከብር የሕግ ማስከበር ሥራውን በንቃት የሚደግፍ የህዝብ አቅም አደረጃጃት መፍጠር እንዲሁም ህጎች ለህብረተሰቡ በተቀላጠፈ መንገድ እንዲታውቁና እንዲሠራጩ ማድረግ ቁልፍ አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

 

በዚሁ መሰረት በፌዴራልና በክልል የሚወጡ ህጎችን የማሰባሰብ፣ የማጠቃለልና አሳትሞ ለተጠቃሚው ማዳረስ ሥራዎች በቋሚነት የሚሠሩበት ሥርዓት በመዘርጋት ከ1934 ጀምሮ አስከ 2010 በጀት ዓመት የወጡ አዋጆች፣ ደንቦችን የማጠቃለልና በማሰባሰብ በዘመናዊ መልኩ በማደራጀት በቀላሉ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ስር ተከናውኗል፡፡

 

የህብረተሰቡ የንቃተ ሕግ ግንዛቤ ለማዳበር የገፅ ለገፅ ትምህርትን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ትምህርት በመስጠት ህብረተሰቡ ሕግ አክባሪና ለፍትህ ሥርዓቱ አጋዥ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል፡፡ የፌዴራል መንግስቱ ህጎች ተግባራዊ መደረጋቸውን አተገባበራቸው ወጥነት ያለው መሆኑንና  የዐቃቤ ሕግ ፍቃደ ሥልጣን አጠቃቀምና ውሳኔ ወጥነት ለማረጋገጥና ሌሎች የሥነ ምግባር ጥሰቶች ለመከታተል የሕግ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ተጠናክረው የሚካሄድ ይሆናል፡፡

 

በብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሀ ግብር በሚመለከት በተባበሩ መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ካውንስል ስብሰባ ላይ በመገኘት ለሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ ገለፃ ተደርጓል፡፡ ከፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለመለየት በፌዴራል ደረጃ ባሉት አምስት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ዳሰሳዊ ጥናት የተደረገ ሲሆን የጥናቱ የግኝት ሪፖርት ተዘጋጅቷል፡፡

 

በሕግ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማሻሻል ልዩ ልዩ በአሳልፎ መስጠት፣ በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትህ ትብብርና በሀገሪቱ ላይ ለሚቀርቡ የተለያዩ ሕግ ነክ ክሶች፣ ጥያቄዎችና አቤቱታዎች ምላሽ የመስጠት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በሙስና  እና በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት ከሐገር የወጡ የአገር ገንዘቦችን ለማስመለስ ከተለያዩ አገራት ጋር ውይይት ተጀምሮ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች  እየታዩ ይገኛል፡፡

 

ከምርመራ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃት ወንጀሎች ላይ በጋራ በመስራት አጥፊዎች ተገቢው ክስ እንዲቀርብባቸውና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የሴቶችና ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ ከኤች አይቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን በህገ መንግስቱና ዓለም ዓቀፍ ስምምነትየተረጋገጠላቸው መብቶችን የማክበር፣ የእኩልነት ተሣትፎአቸውንና ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ እንዲሁም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በተቀናጀ አግባብ የመከላከል ተግባራት ተጠናክረው እንዲከናወኑ ተደርጓል፡

 

ማጠቃለያ

 

በአጠቃላይ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከመጋቢት እስከ መጋቢት ባለዉ የአንድ አመት ጉዞ ዉስጥ የፍትህ ስርአቱን ሪፎርምን በተመለከተ ሲያከናዉናቸዉ ከነበሩት በርካታ ተግባራት ዉስጥ ለማሳያነት ዋና ዋናዎቹን ለማንሳት ተሞክሯል፡፡ ተቋሙ የፍትህ ስርዓቱን የማጠናከርና የህግ የበላይነትን የማክበርና የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ ለማሰቀጠል ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን ወደፊትም የህብረተሰቡን የፍትህ ጥማት ለማርካት በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል፡፡


ለሕግ፣ ለፍትሕ፣ ለርትዕ!!

 


###

Capture 118.JPG