Search

ተቋሙ በአለማቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብት ስምምነቶች ሀገራዊ አፈጻጸምን አስመልክቶ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው

Published: 256 days ago

የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተቋም በአለማቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት ሀገራዊ አፈጻጻምን አስመልክቶ ተጠቃሎ በተዘጋጀ ሁለተኛና ሶስተኛ ሪፖርት ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ በደንበል ቪው ኢንተርናሽናል ሆቴል ውይይት እያደረገ ነው፡፡

 

በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህግ ጉዳዮች ዘርፍ አማካሪ የሆኑት አቶ ተካ ገብረኪዳን እንደገለፁት፤ ሀገራት የፈረሟቸው ወይም የተቀበሏቸው አለማቀፍና ቀጠናዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች በሀገራቱ ላይ የሚጥሏቸው የተለያዩ ግዴታዎች አሉ፤ ከግዴታዎቹ መካከል አንዱ ስለስምምነቶቹ ሀገራዊ አተገባበር የመነሻና በየጊዜው የሚዘጋጁ ወቅታዊ የአፈጻጸም ሪፖርቶችን ማቅረብ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

አክለውም አገራችን ኢትዮጵያ ይህንን ግዴታዋን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዋነኝነት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ስትወጣ መቆየቷን አውስተው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም በአዋጅ ቁጥር 943/2008 መቋቋሙን ተከትሎ በአዋጁ አንቀጽ 6(8)(ሠ) መሰረት ለተቋሙ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች አንዱ የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር አለማቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች አስመልክቶ ሀገራዊ የአፈጻጸም ሪፖርቶችን ማዘጋጀት እንደሆነ ገልፀው በዚሁ መሰረትም አሁን የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አፈጻጸም ረቂቅ ሪፖርት ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

 

በተጨማሪም አቶ ተካ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተቋም በአዋጅ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ ሪፖርቱን ለማዘጋጀት የተሻለ ጊዜ ሆኖ ስላገኝው በተቋም ደረጃ ሪፖርት የማቅረቢያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና የተቃረበባቸውን ስምምነቶችን በመለየት ሪፖርት ለማዘጋጀት ይቻል ዘንድ የሪፖርት ዝግጅት ኮሚቴ አዋቅሮ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ያሉ ሲሆን በሪፖርት ዝግጅቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል ተብሎ ከታመነባቸው ተቋማት ማለትም፡- ሰላም ሚኒስቴር፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፣ትምህርት ሚኒስቴር፣የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ባለሙያዎችን እንዲመደቡ በማድረግ የሪፖርት ዝግጂት ስራ ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል፡፡

 

በሌላ በኩል ደግሞ ለመድረኩ የሁለተኛና ሶስተኛ ዙር ሀገራዊ አፈጻጸም ረቂቅ ሪፖርት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህግ ጉዳዮች ዘርፍ አማካሪ በሆኑት በአቶ አሰግድ አያሌው የቀረበ ሲሆን ሪፖርቱ በውስጡ ያካተታቸውን ሀሳቦች በዝርዝር ለመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸው ፤ሪፖርቱ በሰብአዊ መብት ዙሪያ የመንግስታት ኃላፊነትና ግዴታዎች ምንምን ናቸው፣የሰብአዊ መብት አፈጻጸም ዘገባ የማቅረብ የመንግስታት ግዴታዎች፣አለማቀፍና ቀጠናዊ የስብአዊ መብት ስምምነቶች ምን ምን እንደሆኑ፣የኢትዮጵያ ግዴታ አተገባበር ምን ይመስል እንደነበር፣አለማቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አጠቃላይ ይዘት፣እንዲሁም በአለማቀፍና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ የሚቀርበው ሪፖርት ረቂቅ አዘገጃጀት ይዘት ምን ይመስላል የሚሉት ነጥቦች ተካተው ለመድረኩ የቀረቡ ሲሆን ከውይይት መድረኩም ይጠበቃሉ ተብለው የታሰቡ ውጤቶችም ተመላክተዋል፡፡

 

በመድረኩ ከፌዴራልና ከክልል ተወክለው የመጡ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከሲብል ማህበረሰብ ድርጀቶች እና አጋር የሆኑ የአለማቀፍ ድርጂት ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን በመድረኩም በርካታ ሀሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው ግብአቶች ይሰባሰባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡


###

67183661_2364126637014740_4591811198999068672_n.jpg  66851150_2364126490348088_7311911526263160832_o.jpg