Search

ባለፈው በጀት ዓመት 138 ሚሊዮን ብር በሙስና ወንጀሎች የተመዘበረውን ሀብት በማስመለስ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ መደረጉ ተገለጸ

Published: 126 days ago

በ2011 በጀት አመት በሙስና ወንጀሎች ሀብትን በማስመለስ እና በማስከበር ዙሪያ 138 ሚሊዮን ብር ወደ መንግስት ካዝና ገቢ መደረጉን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተረፈ አሰፋ ገለጹ፡፡

 

ዳይሬክተሩ አያይዘውም ከዚሁ ተግባር ጋር በተያያዘ በመልካም አስተዳደር ላይ በመመርኮዝ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ታግለናል ያሉ ሲሆን፤ ያላግባብ በመንግስት ላይ ኪሳራ ባደረሱ አካላት በዘርፉ የተሰማሩ አቃቤህጎች በተለያዩ የክህሎት ማሻሻያዎች በመታገዝ ምርመራ አድርገው ክስ እንዲመሰርቱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

 

የቀድሞው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 ዓ.ም ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መቀየሩን ተከትሎ፤ከተጨመሩለት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል ምርመራን መምራትና ማስተባበር ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም በአገሪቱ ላይ የተፈጸሙ ከባባድ ወንጀሎች ላይ ምርመራ በመምራትና በማስተባበር በወንጀሉ ላይ የተሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዉ ለአብነትም በሜቴክ፣በዉሀ ስራዎችና ኮንስትራክሽን፣ በመንግስት ግዥ ኤጀንሲ ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ምርመራ ተደርጎባቸዉ ክስ መመስረቱን አውስተዋል፡፡

 

ዳይሬክቶሬቱ የወንጀሉን ዉስብስብት በመረዳትና ትኩረት ሰጥቶ ለመሰራት ያመቺ ዘንድ በሙስና ወንጀል የተገኙትን ሀብቶች የሚያስመልስና የሚያስወርስ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፍትህ አስተዳደር ዘርፍ የሚሰሩ ማስተባበሪያዎችን በማደራጀት በበጀት አመቱ በሙስና ወንጀሎች ዙሪያ ስኬታማ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር መቻሉን አቶ ተረፈ አክለዉ ገልፀዋል፡፡

 

በሙስና ወንጀል የተሳተፉ አካላት በህግ ተጠያቂ ሆነዉ ውሳኔ ከተላለፈባቸዉ በኋላ ገንዘብ መልሰዉ ክሳቸዉ ይቋረጣል ይህ ከህግ አንፃር እንዴት ይታያል ብለን ለዳይሬክተሩ ላነሳንላቸዉ ጥያቄ የሙስና ወንጀል ዋና ትኩረቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ገንዘብን መከተል (follow the money principle) በመሆኑ የሙስና ወንጀል አስተዳደሩንና የወንጀል ፍትህ አስተዳደሩን አደጋ ላይ የማይጥል ከሆነ ገንዘቡን ተመላሽ በማድረግ ሰዎች የሚለቀቁበት አሰራር ህጋዊ መሰረት ያለዉ መሆኑን ካብራሩ በኋላ የፍርድ ቤትንና የዐቃቤ ህግ ጊዜን ታሳቢ በማድረግ ክሳቸዉ እንዲቋረጥ ማድረግ ይቻላል ሲሉ አክለዋል፡፡

 

ከዚህም ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ከለዉጡ ማግስት የሰማዉን ብስራት ቶሎ ቶሎ ማወቅ በመፈለጉ የሙስና ትግሉ ተዳክሟል የሚሉ ትችቶችን ሲያነሳ ይስተዋላል ተብሎ ለተነሳዉ ጥያቄ የሙስና ትግሉ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉንና ምርመራዎች ጊዜን መሰረት አድርገዉ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ የሚከናወን ከመሆኑም በተጨማሪ በትኩረትና በጥንቃቄ መመራት ያለበት በመሆኑ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑ መረጃዎች የመዘግየታቸዉ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ዳይሬክተሩ በ2012 በጀት አመት ሰፊ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱንና በተለይም በሀብት ማስከበርና ማስመለስ እንዲሁም ማስወረስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

 

በመጨረሻም የሙስና ወንጀል ዉስብስብ እንደመሆኑ መጠን የፍትህ አካላት ጉዳይ ብቻ ሊሆን አይገባም ካሉ በኋላ የህብረተሰቡን ሰፊ ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ወንጀልን በማጋለጥ የራሱን ሚና መጫዎት እንደሚገባዉ ከገለፁ በኋላ ምስክርነትን ከመስጠት ጋር ተያይዞም ጥሩ ቁርጠኝነት ያላቸዉ አካላት እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒዉ ሰፊ ክፍተት ያለ በመሆኑ በዚህ ላይ የሚመለከታቸዉ ባለ ድርሻ አካላት በባለቤትነት መንፈስ ሊሰሩና ሊተባበሩ ይገባል ሲሉ መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡


###

70599098_535711310515476_2448563204796710912_n.jpg  70494040_741288916296410_6062490125219135488_n.jpg