Search

2011 በጀት አመት በተለያዩ ክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች ላይ ተሳትፈዋል በተባሉ 1,323 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱ ተገለጸ

Published: 125 days ago

በ2011 በጀት አመት በተለያዩ ክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች ተሳትፈዋል በተባሉ 1,323 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱን በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተደራጁ ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ ገለጹ፡፡

 

እንደዳይሬክተሩ ገለጻ በበጀት አመቱ በሁሉም ክልሎች በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ 1,229 ሰዎች ህይዎታቸው ያለፈ ሲሆን፤በ1,393 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስ በ19 ሰዎች ላይም የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

 

በተያያዘም 2,290,490,159. /ሁለት ቢሊየን ሁለት መቶ ዘጠና ሚሊየን አራት መቶ ዘጠና ሺ አንድ መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ብር ገደማ የሚገመት የዜጎች ንብረት የወደመ ሲሆን፤1,200437(አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ አራት መቶ ሰላሳ ሰባት) ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸውና ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህም ጋር በተያያዘ በዚህ ድርጊት ላይ ተሳታፊ በነበሩ 1,323 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቶ ከእነዚህ መካከል 645 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑንና 667 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ያልተያዙ ሲሆን፤የ10 ተጠርጣሪዎች ክስም በምህረት መነሳቱን ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

 

በሌላ በኩል በአማራ ክልል በጃዊ ወረዳና በመተክል ዞን ፤በጎንደርና አካባቢው በተፈጠረ ሁከትና ብጥብጥ፤በሰሜን ሸዋ አስተዳደር እንዲሁም በቤንሻጉል ጉምዝ ክልል ከማሻ ዞን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎችና የዚሁ ዞን አጎራባች በሆነው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞን በተለያዩ ቀበሌዎች ላይ በተፈፀመ ብጥብጥና ሁከት በአሶሳ ዞን አራት ወረዳዎች ውስጥ በኦሮሚያና በበርታ ብሄረሰብ መካከል በተፈጠረ ግጭት ተሳታፊ የነበሩ በአጠቃላይ 1647 ተጠርጣሪዎች ተለይተውና አስፈላጊው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ተሰባስበው እስካሁን ድረስ 185 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ የተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ሀላፊዉ ቀሪዎችን 1462 ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የማፈላለግ ስራም እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

 

በመጨረሻም አቶ ፍቃዱ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረግ እንቅስቃሴ ዙሪያ የሚስተዋለው ክፍተት አስመልክቶ መፍትሔ ያሉትን ሀሳብ ሲጠቁሙ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከፍትህ አካላት ጎን በመቆምና ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ በመስጠት በኩል በጉዳዩ ላይ በባለቤትነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽእኖት ሰጥተው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 


###

71402340_2484762288284507_7598625499786510336_n.jpg