Search

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የ100 ቀናት ዕቅድ ተግባራት አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ተገለጸ

Published: 123 days ago

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የ100 ቀናት ዕቅድ ተግባራት አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን በተቋሙ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ገለጹ፡፡

 

ተቋሙ 2011ዓ.ም አዘጋጅቶ በተገበራቸው የ100 ቀናት ዕቅዶች የሕግ የበላይነት እና የፍትሕ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር የሚያስችሉ የሕግና የፍትህ የሪፎረም ስራዎች አከናውኖ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን የገለጹት ዳይሬክተሩ በያዝነው ዓመትም በመጀመርያ ሩብ የ100 ቀናት ዕቅዱን በአግባቡና በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት በትኩረት ይከናወናል ብለዋል፡፡

 

አቶ ዝናቡ አክለውም በሩብ አመቱ የ100 ቀናት ዕቅዱ ሊተገበሩ ከተያዙ ዋና ዋና ተግባራት መካከል፤ በተመረጡ ከባድ ወንጀሎች ላይ የመርማሪዎችንና የዐቃብያነ ህጎችን የምርመራ አቅም ለማሳደግ የሚያስችል አለም አቀፍ ልምድ ባላቸው ባለሞያዎች ስልጠና መስጠት፣ የወንጀል መዛግብት አያያዝና አስተዳደር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስርዓት ለመቀየር የተጀመረውን የወንጀል መዛግብት አስተዳደር መረጃ ስርዓት (criminal record management information system) የሶፍትዌር ግንባታ ስርዓቱን ማጠናቀቅ፣ በምስክሮችና ተከሳሾ ምክንያት የሚቋረጡ መዛግብትን ምክንያት በጥናት በመለየት ስር ነቀል የአሰራር ስርአት እንደሚዘረጋ ገልጸዋል፡፡

 

በተጨማሪም ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ የሠማያዊ ልብ (Blue Heart Campaign) ንቅናቄ በርካታ ሰዎች በተገኙበት እንዲካሄድ ማድረግ እና የፍልሰት አስተዳደር ፖሊሲ ዝግጅት ለማካሄድ የሚያግዝ የፍልሰት አስተዳደር ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት እንዲሁም በሙስናና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት የተመዘበረ የህዝብ ሐብት በአስተዳደራዊ ሂደት አሊያም በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገኘውን ሀብት የመለየት፣ የማሳገድና ክስ የመመስረት ስራ እንደሚሰራም ጭምር አውስተዋል፡፡

 

በሌላ በኩል በመንግስት እና በተለያዩ የግል ባንኮች ላይ የተፈጸሙ የምዝበራና የሙስና ወንጀሎችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አጠቃላይ የምርመራ ስራዎች እንዲጠናቀቁ ማድረግና ምርመራቸው በተጠናቀቁት መዛግብት ላይ አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት፣ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ግጭት በማስነሳትና በግጭት በመሳተፍ እንዲሁም በሙስና ወንጀልች ተከሰው በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተከሳሾችን በመለየት ለፌዴራል ፖሊስና ለክልሎች ለሚመለከታቸው አካላት መስጠትና ክትትል በማድረግ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረግ በዕቅዱ የተያዘ ሲሆን ከብሔር ግጭትና ከሙስና ጋር በተገናኘ በተከሰሱበት ወንጀል ከሀገር ስለመውጣታቸው ማስረጃ የቀረበባቸውን ተከሳሾችን ያሉበትን ሀገር በመለየት የቀረበባቸውን ክስና ማስረጃ በማዘጋጀት ተላልፈው እንዱሰጡ ከሀገሪቱ ጋር ድርድር እንደሚደረግም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

 

የተለያዩ ህጎችን ከማርቀቅ ጋር በተያያዘም የወንጀለኛ ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ፣ የጥብቅና ፈቃድ አስተዳደር ሕግ፣ የሚዲያ ሕግ እና የአስተዳደርና የሕግ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት ሕግን በተመለከተ የቀሩ ስራዎችን አጠናቆ ለሚንስትሮች ምክር ቤት የማቅረብ ስራ በሩብ ዓመቱ የ100 ቀናት ዕቅድ በሚከናወኑት ተግባራት መያዙን የህዝ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ገልጸዋል፡፡


###

52898317_2133343180093088_4237424999205437440_n.jpg