Search

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ግምገማዊ ውይይቱን እንደቀጠለ ነው

Published: 54 days ago

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንደ ሀገር የተጀመረውን ሁለንተናዊ ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የ2012 በጀት ዓመት ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጀቶ በየደረጃው ካሉ አመራሮችና ሰራተኞች ጋር ምክክር በማድረግና መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ከሐምሌ 01/2011 እስከ መስከረም 30/2012 በተደረገው የ1ኛ ሩብ ዓመት የአፈፃፀም ጉዞ በርካታ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል፡፡

 

በነበረው የ1ኛ ሩብ ዓመት የአፈፃፀም ጉዞ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ዜጎች በሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቀጥተኛ ተሣታፊ እንዲሆኑ ሰፊ ጥረት የተደረገ ሲሆን በተለይም የሲቪክ ማህበራት፣ የህዝብ አደረጃጀት ተወካዮች፣ የሕግ ባለሞያዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንደ አዲስ እየተዘጋጁና እየተሻሻሉ ባሉ ሕጎች ዙሪያ በቀጥታ እንዲወያዩ በማድረግ ግብአቶችን የማሰባሰብና ሕጎቹን የማዳበር ሥራ ማከናወን ተችሏል፡፡

 

በስራ ላይ ስላሉ ሕጎች ዜጎች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ የራሳቸውን መብት ከማስከበር ባለፈ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ማለትም በህግ የበላይነት መርሆች፣ በአለም አቀፋዊና ሀገር አቀፋዊ ሕጎች አጠባበቅና አተገባበር፣ በህጻናት ህገ-ወጥ ዝውውርና ጉልበት ብዝበዛ፣ በወንጀል ጉዳይ ተከሳሽ በሌለበት ስለሚታይበት ሁኔታ፣ በሀሰተኛ ምስክርነትና ህጋዊ ተጠያቂነት፣ በአለም አቀፍ ውሎች ዝግጅት እና የግልግል ዳኝነት መርሆዎች እንዲሁም በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን መሰጠት መቻሉን ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡

 

በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶች አቅመ ደካሞች እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናት ተጠቃሚ እንዲሆን ከማስቻላቸው አንጻር በሩብ ዓመቱ ለ189 ዜጎች ነፃ የፍትሐብሔር ህግ ምክርና ጥብቅና አገልግሎት መስጠት የተቻለ ሲሆን 7,249 ለሚሆኑ የተለያዩ አቤቱታ አቅራቢዎችም ቀልጣፋ አገልግለት መስጠት ተችሏል፡፡

 

የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱንና የሕዝብ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በ12‚274 መዛግብት ላይ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ተደርጓል፡፡

 

የምርመራ መዛግብትን በማጥራት ረገድም ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ ጋር ተቀራርቦ በመስራት ለውሳኔ በቀረቡ መዛግት ላይ ውሳኔ ማሰጠት መቻሉንና የሚፈለጉ ማስረጃዎችን ሟሟላት እንዲቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱ በጥንካሬ ተገምግሟል፡፡

 

በነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይቱ ቀጥሎ በአፈጻጸም ወቅት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን እንዲሁም የታዩ ክፍተቶችን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች እየተቀመጡ ሲሆን በነገው እለትም በተቋሙ በ10 አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡


###

77423140_2625202984240436_1776026679781621760_n.jpg