Search

በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችንና ለጥቃት አጋላጭ የሆኑ ጎጂ ድርጊቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ተገለፀ

Published: 113 days ago

በኢፌዲሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ጽህፈት ቤት በአየር ጤና ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች በሴቶችና ህፃናት የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ስልጠና የሰጠ ሲሆን በስልጠናውም ተማሪዎች በአካባቢያቸው በሴቶችና ህፃናት ላይ ፆታዊ ጥቃት እና ለጥቃት አጋላጭ የሆኑ ጎጂ ድርጊቶች ሲፈፀሙ በጋራ መከላከል እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

 

በኢፌዲሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ጽህፈት ቤት የሴቶችና ህፃናት አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሪት ጥሩዘር በስልጠናው ላይ እንደገለፁት በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት በአንቀጽ 35 ላይ የሴቶችን መብት በተለየ የtደነገገ ሲሆን ሴቶች በህገ-መንግስቱ የተረጋገጡላቸውን መብቶች በመጠቀም ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ፣ በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻ ውስጥና በፍቺ ጊዜ፣ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው በህገ-መንግስቱ በመደንገግ ለሴቶች መብት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

 

አስተባባሪዋ እንዳሉት በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች የሚፈፀሙባቸዉ በአብዛኛዉ ለእነሱ ቅርብ በሆኑ ግለሰቦች አማካኝነት እንደሆነ እና ጥቃቱም በቤት ዉስጥ ከቤት ዉጭ እየተፈፀመ ያለ መሆኑን፣ ጥቃቱ የተፈፀመባቸዉም የደረሰባቸዉን ጉዳት ከማሳወቅ ይልቅ ዝም በማለታቸዉ ለተጨማሪ የስነ-ልቦና ጉዳት እየተጋለጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

 

አያይዘዉም በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የግብረ ስጋ ድፍረት በደል፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ጠለፋ እና ፆታዊ ጥቃትን በኢፌዲሪ የወንጀል ህግ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ድርጊቶችን እና የሚያስከትሉትን ቅጣቶች እንደ ወንጀል ደረጃቸው የሚያስቀጣ መሆኑ በህግ ተቀምጧል ያሉ ሲሆን በሴቶች ላይ ጥቃት በሚፈፀምበት ጊዜ ተበዳይዋ በአካል ቀርባ እንዲሁም ህብረተሰቡ አቅራቢያዉ ላለ ፖሊስ ጣቢያ፣ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይም ሴቶችና ህፃናትን በሚመለከቱ በየወረዳዎች ባሉ ተቋማት ላይ ቀርቦ ጥቆማ ማድረግ አለበት፣ አጥፊዎችም ወደ ጥቃት እንዳይገቡ ራሳቸውን መቆጣጠርና ማሰብ ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

በኢፌዲሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ጽህፈት ቤት ዐቃቤ ህግ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት ጣሰው የህፃናት መብትን አስመልክቶ ሲናገሩ በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ህጎች የህፃናት መብት ህጎችን ተቀብላ ከማፅደቋ ጋር ተያይዞ የአለም አቀፍ ህጎች የህጋችን አካል እንደሆነ ህገ-መንግስቱ አስቀምጧል ያሉ ሲሆን ህፃናት በህይወት የመኖር መብት፣ ወላጆችን ወይም በህግ የማሳደግ መብት ያላቸው ሰዎችን የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት፣ ጉልበታቸውን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርታቸው፣ በጤናቸው፣ በደህንነታቸውና በአካላቸው ላይ ከሚፈፀም ኢ-ሰብአዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን መብቶች አሏቸው ብለዋል፡፡

 

እንደ ወ/ሮ ትዕግስት ገለፃ በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ በህፃናት አካል ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ በህፃናት ስነ-ልቦና ላይ ሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ የግብረ ስጋ ድፍረት፣ የግብረ ሰዶም ወንጀሎችና ሌሎችንም በመደንገግ ቅጣትን የሚያስከትሉ መሆናቸውን ህጉ የደነገገ ሲሆን እነዚህ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ በጋራ መስራት ከእኛ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በስልጠናውም ከተማሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በተነሱት ሀሳቦች ላይም የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ማብራሪያና ሰጥተዉበት ስልጠናው ተጠናቋል፡፡

 


###

79301473_604814090324642_79961210035896320_n.png