Search

ሕገወጥ የውጭ አገር የስራ ስምሪትን መከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑ ተገለፀ

Published: 86 days ago

በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፀረ-ህገወጥ ሰዎች ዝውውር ግብር ኃይል ጽ/ቤት ባለድርሻ አካለት በተገኙበት የውጭ አገር የስራ ስምሪት አፈፃጸም፣ የፍልሰት ጉዳዮች በዘላቂ የልማት ግቦችና አገር አቀፍ ዕቅድ ጋር በተያያዘ ምን ያህል ተካተዋል በሚል ለ2 ቀናት ውይይት ተካሄደ፡፡

 

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ የሆኑት አቶ ዘሪሁን የሽጥላ የስራ ስምሪት አፈፃጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት በአገራችን ለረዥም አመታት የውጭ አገር የስራ ስምሪትን የሚመራና የሚቆጣጠር የተጠናከር ሕግ፣ አሰራርና አደረጃጀት ባለመኖሩ ዜጎች በህገ-ወጥ የሰራ ሰምሪት የአካልና የህይወት ጥቃት ይደርስባቸው እንደነበር ጠቁመው፣ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ አዋጅ ቁጥር 923/2008 በማውጣት ሕግዊ አሰራር የተከተለ የውጭ አገር የስራ ስምሪት እንዲተገበር በተጠናከር ሁኔታ እየተሰራ መሆን ተናግረዋል፡፡

 

አቶ ዘሪሁን አክለውም በአዲሱ አዋጅ ሰራተኛን በውጭ አገር ለስራ ማሰማርት የሚቻለው በኢትዮጵያና በተቀባይ ሀገር መካከል የሁለትዮሽ ስምምነት ብቻ ሲሆን መንግሰት የሁለትዮሽ ስምምነት ካልፈፀመባቸው አገራሮች ጋር ምንም አይነት የስራ ስምሪት እንደማይደረግ እና ውጭ አገር በመሄድ መስራት የሚፈልጉ ዜጎች ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቁ፣ ለሚሰማሩበት የስራ መስክ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የያዙ፣የጤና ምርመራ ውጤት እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የጸደቀ የስራ ውል ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

 

አቶ ዘሪሁን አያይዘው በግማሽ በጀት አመት የተከናውኑ ተግባራትን ያቀረቡ ሲሆን 265 መንግስታዊና የግል ማሰልጠኛ ተቋማት ውጭ አገር ሄደው መስራት ለሚፈልጉ ዜጎች የሙያ ስልጠና እየሰጡ መሆኑን፣ 9,552 ዜጎች እስካሁን መሄዳቸውን፣ ሕጋዊ አሰራርን ተከትለው በማይሰሩና በቀረበባቸው አቤቱታ መሰረት 2 ኤጀንሲዎች በሕግ እንዲጠየቁ፣41 ኤጀንሲዎች በማስጠንቀቂያ እና 15 ኤጀንሲዎች ምክር የታለፉ መሆኑን ጠቅሰው የሁለትዮሽ የስራ ስምምነት የተደረገባቸው አገራሮችም ጆርዳን፣ኳታር፣ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

 

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአዲሱ አዋጅ ይዘት፣ የስራ ስምሪት እንዲሁም የተከናወኑ ተግባራት በተመለከተ ክፍተቶችን በመጠቆም፣ጥያቄና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ መድረክ መሪው ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ሕገ-ወጥ የውጭ አገር የስራ ስምሪትን መከላከል የአንድ ተቋም ተግባር ሳይሆን የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

 

የፀረ-ህገወጥ ሰዎች ዝውውር ግብር ኃይል ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፈትያ ሰይድ የቀረቡውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ በውጭ አገር የስራ ስምሪት የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት ከትብብርና ቅንጅት ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችን በማስተካከል፣ ሁሉም የግብረ ኃይሉ አባላት የተጠያቂነት አሰራርን በመዘርጋት፣ በመንግስት የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት በትኩረት እንዲሁም በባለቤትነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባና የውጭ አገር የስራ ስምሪትን በማጠናከር፣ ህገ-ወጥ የስራ ስምሪትንና ህገ-ወጥ የሰዋች ዝውውር በመከላከል ዜጎችን ከጉዳት መጠበቅ እንደሚገባም በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

 

በሁለተኛው ቀን ውይይት መድርክ የፍልሰት ተዛመጅ ጉዳዮች በዘላቂ የልማት ግቦች፣በአገር አቀፍ ዕቅድ፣ፖሊሲዎችና ስትራቴጂወች ላይ ምን ያህል እንደተካተቱ የሚዳስስ ረቂቅ ጥናታዊ ጹሁፍ በIዐM አማካኝነት በዶ/ር ባምላክ አላምረው ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡


###

82066193_2727083174052416_3914116783333703680_o.jpg