Search

በመረጃ ነፃነትና በኮምፒውተር ወንጀል ረቂቅ አዋጆች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት እና የዘርፋ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሄደ

Published: 66 days ago

በኢትዮጵያ የሕግና የፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት የሚዲያ ጥናት ቡድን የመረጃ ነፃነትና የኮምፒውተር ወንጀል ረቂቅ አዋጆች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ጥር 23/2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

 

የሚዲያ ጥናት ቡድን አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ጎሹ በውይይቱ መክፈቻ ወቅት እንደተናገሩት የመረጃ ነፃነትና የኮምፒውተር ወንጀል ረቂቅ አዋጆችን በሚፈለገው መልኩ አርቅቆ ሥራ ላይ ለማዋል ጠቃሚ የሆኑ ግብዓቶችን የማሰባሰቡ ሥራ እስከአሁን ሲካሄድ እንደነበረ ጠቁመው ይህ መድረክም ከባለድርሻ አካላትና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት በማድረግ ተጨማሪ ምክረ ሀሳቦችን ለማግኘት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

የሚዲያ ጥናት ቡድኑ አባልና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር መሰንበት አሰፋ በበኩላቸው እንደተናገሩት አገራችን በለውጥ ሂደት ላይ ያለች በመሆኗና መንግስት ካሳየው ቁርጠኝነት አኳያ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች እየተሸሻሉ ሲሆን ከነዚህ መካከል የኮምፒውተር ወንጀል ረቂቅ አዋጅ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

አያይዘውም የኮምፒውተር ወንጀል አዋጁ ሦስት ይዘቶች ያሉት ሲሆን እነሱም በኮምፒውተር ሲሰተም የሚፈፀም ወንጀል፣ በግል የሚፈፀም ወንጀል እና ከይዘት ክልከላ ጋር በተያያዘ የሚፈፀም ወንጀል ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል በማለት ተናግረዋል፡፡

 

በሌላ ብኩል የሚዲያ ጥናት ቡድኑ አባል የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ እንደተናገሩት የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ዘዋጁ መንግስትን ለመቆጣጠር የምንጠቀምበት መሣሪያ ሳይሆን የመንግስትን አሰራር ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግና ሙስናን ለመከላከል የሚያገለግል ሆኖ ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ የሚፈጠሩ አሉባልታዎችንና ውዥንብሮችን ለመከላከል ይረዳል ካሉ በኋላ አዋጁን ለማስፈምም ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነ ነፃና ገለልተኛ ኮሚሽን ሊቋቋም እንደሚገባ በረቂቅ አዋጁ የተካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


###

83954347_2763429190417814_3763959083078516736_o.jpg